ንግድ ባንክ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ያደገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

በአሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ እየተመራ ከሁለተኛው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ውድድር ወደ ዋናው ሊግ ያደገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን የኪቲካ ጅማ፣ ቢኒያም ጌታቸው እና ተስፋዬ ታምራትን ዝውውር የቋጨ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

ምንም እንኳን መልቀቂያ ከቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምጥቶ ውሉ በፌዴሬሽን ባይፀድቅም ከክለቡ ጋር ስምምነት የፈፀመው ተጫዋች ሱሌይማን ሀሚድ ነው። የቀድሞ የአዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች የነበረው ሱሌይማን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስቶ እንደነበር አይዘነጋም።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ገናናው ረጋሳ ነው። የቀድሞ የወልዋሎ ዓ/ዩ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና መቻል የመስመር ተከላካይ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ካሳለፈ በኋላ ዳግም በሊጉ ለመጫወት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምርቷል።